በሚኒስቴር መ/ቤቱ በከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት በኩል በአማካሪ ሲከናወን የቆየዉ የባህርዳር ከተማ ልዩ ባህሪ ያላቸዉ ንብረቶች ልየታ፣ በGIS ካርታ ማስፈር እና ግመታ ጥናት ተጠናቆ ለከተማ አስተዳደሩ የጥናት ሰነድ ርክክብ ተደረገ
በሚኒስቴር መ/ቤቱ በፕሮጀክት ጽ/ቤቱ በኩል የከተሞችን ገቢ ለማሳደግ ከሚከናወኑ ስራዎች ዉስጥ አንድ የሆነዉን ልዩ ባህሪ ያላቸውን ንብረቶች ልየታ፣ በጂኣይኤስ ካርታ በማስፈርና የግመታ ጥናት ላላፉት 12 ወራት በባህርዳር ከተማ አስተዳደር በአማካሪ ሲያከናዉን ቆይቶ ጥር 27 ቀን 2014 ዓ.ም ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጋር የሰነድ ርክክብ አደረገ፡፡
በሰነድ ርክክቡ ወቅት በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒሰቴር የከተማ አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ሚኒሰቴር ዴኤታ የሆኑት ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን እንደገለጹት ይህ ጥናት ዘመናዊ የንብረት ግብር አሠራር እና ስሌት ትልቅ ግብዓት ከመሆኑም በላይ በከተሞች የንብረት ግብይት ስርዓቱ ሳይንሳዊ የግምት መረጃን መሰረት አስርጎ እንዲፈጸምና ከዚህም ከተሞች ማግኘት ያለባቸዉን ገቢ ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታዉ አክለዉም የከተሞችን ጠቅላላ የካፒታል መጠንና የመበደር አቅም ለመወሰን የሚያስችሉ፣ ልዩ ባህሪ ላላቸው ንብረቶች ግመታ እሴትና ለካሳ ክፍያ መነሻነት እንዲሁም ልዩ ባህሪ ያላቸው ንብረቶች ባለቤቶች ንብረቱን በዋስትና በማሳዝ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ ያለዉ እንደሆነና ጥናቱ በአጠቃላይ ሲታይ ለከተሞች ዋነኛ የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ከፍተኛ ድርሻ ያለዉ በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ይህንን ጥናት ወደ ተግባር እንዲያወርደዉ አስገንዝበዋል፡፡
በሌላ በኩል በርክክብ መድረኩ የተገኙት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ክቡር ዶ/ር ኢብራሂም መሐመድ በሰነድ ርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ጥናቱ የመጀመሪያና ፈርቀዳጅ በመሆኑ ጥናቱ ለከተማ አስተዳደሩ ከሚያስገኘዉ ጥቅም በላይ ባለሀብቶች ንብረታቸው ተለይቶ በጂአይኤስ ሲቀመጥላቸውና ግምት ሲሰራለት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እጅግ የጎላ እንደሆነ በመግለጽ በባህርዳር ከተማ የተጠናዉ ጥናት ወደ ተግባር እንዲወርድ ክልሉ አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግና በባህርዳር ከተማ ትግበራ ዉጤት መነሻነት መሰል ጥናቶች በክልሉ በሚገኙ ሌሎች ከተሞች መስፋት እንደሚገባዉና ጥናቱ ተግባር ላይ እንዲውል በየደረጃው ያለ አመራርና ባለሙያ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እደሚገባ ጠቁመው ሚኒሰቴር መ/ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ እዲቀጥል አደራ ብለዋል፡፡
በዕለቱ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር ዶ/ር ድረስ ሳህሌ በበኩላቸው ይህ ጥናት በከተማዉ መከናወኑ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዉ በጥናቱ ዉጤት የተገኙ ልዩ ባህሪ ያላቸው ንብረቶች ጥቅል ግመታ፣የትግበራ ስልቶችንና የተቀመጡ ምክረ ሀሳቦችን በከተማዉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣመር በተገቢዉ ስራ ላይ በማዋልና ከዚህ ረገድ ከተማዉ ያለዉን የገቢ አቅም በማሳደግ እያደገ የመጣዉን የነዋሪዎች የመሰረተ-ልማት የመልማት ፍላጎት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ለመቅረፍ የጥናት ዉጤቱ በተገቢዉ ተግባር ላይ እንደሚዉል ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም በሚኒሰቴር መ/ቤቱ የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ስራስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ ዚነት ኢብራሂም በበኩላቸው ከተሞች ለነዋሪዎች የመሰረተ ልማት እንዲሁም የዘመነና የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ በገቢ እራሳቸዉን እንዲችሉና ከድጎማ ጠባቂነት እንዲወጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል::

